እግዚአብሔር ፈጣ ሪ ነው። ነገር ግን ፈጣሪ ብቻ አይደለም። አዳሽም ነው! የፈጠረው ቢበላሽ ይሠራዋል፣ ቢሰበር ይጠግነዋል፣ ቢጠፋ ይመልሰዋል፣ ቢያረጅ ያድሰዋል፣ ቢሞት ያስነሳዋል፣ ለዚህ ነው፣ እግዚአብሔር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን አዳሽም ነው የምንለው። ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ የሚያሳየን ይህንኑ ነው። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድር ፈጠረ” ካለን በኋላ ምድርን የገጠማትን መበላሸት “ምድርም ባዶ ነበረች፣ አንዳችም አልነበረባትም፣ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበር” በማለት ያስነብበናል። ሆኖም ወዲያውኑ ፍጥረቱ የተበላሸበት አዳሹ እግዚአብሔር ሲነሳና በቃሉና በመንፈሱ ምድርን ለስድስት ቀናት ሲያድስ፣ በሰባተኛውም ቀን ሲያርፍ ያሳየናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በተሐድሶ የታሪክን ሀ ሁ የሚጀምር ብቻ ሳይሆን በተሐድሶ የታሪክን ሂደት የሚደመድም የተሐድሶ መጽሐፍ ነው። “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም።… በዙፋንም የተቀመጠው፦ እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።” የዮሐንስ ራዕይ 21፥1፣ 5

እግዚአብሔር አሁንም በማደስ ሥራ ላይ እንደ ሆነና የዕደሳው መጠናቀቅ ብሥራት የጌታ ዳግም መምጣት እንደ ሆነ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ላይ እንዲህ በማለት ነግሮናል፦ “እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው፥ ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና።” ሐዋ.ሥራ 3፥21 እግዚአብሔር ሁሉን የማደስ ዕቅድ ቢኖረውም የሚጀምረው ከሌላው ፍጥረት ሳይሆን ከሰው፣ ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ፣ ከሥጋ ሳይሆን ከመንፈስ ነው። ስለዚህ አንተ፣ አንቺ፣ እርሶ እና እኔ የዚህ የማደስ ሥራው ማዕከል ነን። ሥራውን መንፈሳችንን በማደስ ጀምሯል፦ “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም” ቲቶ 3፥5። አንድ ቀን ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን በመለወጥ ይለውጠዋል። እስከዚያው ግን በእያንዳንዱ ዕለት አእምሯችንን በማደስ እየቀጠለው ይገኛል። ትልቁ ጥያቄ ይህ በሕይወታችን የሚሠራው የእግዚአብሔር የማደስ ሥራ ምን ያህል ገብቶናል? ምን ያህልስ ራሳችንን በመስጠት እየተባበርን ነው? የሚለው ነው። የመንፈሳችን መታደስ ቅጽበታዊ ነበር፦ “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” ዮሐ. 3፥8። የሥጋችንም መታደስ ቅጽበታዊ እንደሚሆን ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፎልናል፦“እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።” 1ቆሮ.15፥51-52። ነገር ግን የነፍስ መዳን ተብሎ የሚጠራው የአእምሮ መታደስ ጊዜ ፈጅ ነው። ከዳንበት ጊዜ አንስቶ ወደ ጌታ እስከምንሄድበት ወይም ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ያለ ማቋረጥ የሚከናወን ሂደት ነው። መንፈሳዊ እንሁን ሥጋዊ፣ ሰማያዊ እንሁን ምድራዊ፣ ክርስቶስን እንምሰል አዳምን የሚለካው አእምሯችን በታደሰበት ልክ ነው። ዳግም ከተወለድን በኋላ በምድር ላይ የምንኖራት እያንዳንዷ ቀን ከተጠቀምንባት የመዳን ቀን፣ የመታደስ ቀን ናት! አእምሯችን ከታደሰ ክርስቶስን እንመስላለን። የሚያድስ እግዚአብሔር ነው፤ ነገር ግን ለመታደስ መፈለግና ራስን መስጠት፣ መታዘዝና እሺ ማለት የእኛ ድርሻ ነው። እግዚአብሔር ሁሌም ዝግጁ ነው። እኛስ? 2013 ዓ.ም (2020/21) የመታደስ ዓመት ይሁንልን!

በ 2012 በአካል በመገኘት አገልግሎትና ሥልጠና የተሰጠባቸው ከተሞችና ስቴቶች፦

ሚሊዋኪ፣ ዊስኮንሲን

ኦክላንድ፣ ካሊፎርኒያ

ኦሬንጅ ካውንቲ፣ ካሊፎርኒያ

ፖርትላንድ፣ ኦሪገን

ሲያትል፣ ዋሽንግተን

ቦስተን፣ ማሳቹሰትስ

ናሽቪል፣ ቴኔሲ

ፌርፋክስ፣ ቨርጂኒያ

ዋሽንግተን ዲ.ሲ

ሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ

ላንካስተር፣ ፔንሴልቫኒያ

ሻርለት፣ ኖርዝ ካሮላይና

ከመጋቢት ወር ጀምሮ ኮቪድ-19 በዓለም ላይ ይልቁንም በአሜሪካ ባስከተለው ተጽዕኖ
ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ማገልገል ስላልተቻለ። አገልግሎቱ ባጠቃላይ
ወደ ቴሌ ኮንፈረንስ እና ወደ ዙም ተቀይሯል። በዚህም፦

ለንደን፣ ዩናይትድ ኪንግደም = 3X

ዱባይ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ = 4X

ኤድመንተን፣ ካናዳ

ቶሮንቶ፣ ካናዳ 2X

ዴንቨር፣ ኮሎራዶ 5X

ካንሳስሲቲ፣ ካንሳስ

ሎስአንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ 4X

ሳንሆዜ፣ ካሊፎርኒያ 2X

ፊላደልፊያ፣ ፔንሴልቬኒያ 2X

ላንካስተር፣ ፔንሴልቬኒያ 3X

ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሜሪላን 7X

ጂዳ፣ ሳዑዲ አረቢያ 2X

ናሽቪል፣ ቴነሲ 4X

ሚኒያፖሊስ፣ ሚኒሶታ

ሚሊዋኪ፣ ዊስኮንሰን 2X

አሌክሳንደሪያ፣ ቨርጂኒያ 5X

ሲያትል፣ ዋሽንግተን 3X

ባልቲሞር፣ ሜሪላንድ 3X

ኦንታሪዮ፣ ካናዳ

ላስቬጋስ፣ ኒቫዳ 4X

ሂውስተን፣ ቴክሳስ 2X

ሰፊ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን መጠኑ ኮቪድ-19 ከመከሰቱ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በሁለት እጥፍ ይበልጣል።

  • ባለፉት 12 ዓመታት ያለ አንዳች መቋረጥ በሣምንት አራት ጊዜ (በመደበኛ፦ ሁለት ጊዜ፣ በድጋሜ፦ ሁለት ጊዜ) በኤልሻዳይ ቴሌቪዥን ኔትወርክ “ዞዊ ቲቪ” በሚል መጠሪያ የሚተላለፈው ፕሮግራም በዚህም ዓመት በሥኬት ለ ሁለት መቶ ስምንት ጊዜ ተላልፎ በብዙ ሥፍራዎች በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ በብዙ መቶ ሺህ ቤቶች ውስጥ ታይቷል።
  • ማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ማለትም የዩቲዩብ ቻናልና የፌስቡክ ፔጅን በመጥቀም በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን በአገር ውስጥ እና በዓለም ዙሪያ መድረስ ተችሏል። የዩቲዩብ ቻናላችን በየወሩ ከአንድ ሚሊዮን ደቂቃዎች በላይ የሚታይ ሲሆን የፌስ ቡክ ፔጃችን በየወሩ ከመቶ ሺህ በላይ በሆኑ ሰዎች በየወሩ ይጎበኛል። የዩቲዩብ ቻናላችን ውስጥ ከሦስት መቶ የሚበልጡ የቪዲዮ ትምህርቶች የሚገኙ ሲሆን በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል።
  • ዘወትር ረቡዕ ምሽት ለአንድ ዓመት ያለመቋረጥ በተከታታይ “የሚሻል፣ የሚበልጥና የሚልቅ” በሚል ርዕስ የተላለፈው የዕብራውያን መልዕክት ትምህርት በዓለም ዙሪያ ለብዙዎች በረከት ሆኗል።
  • ከዓለም ዙሪያ በኢሜል፣ በበስልክ፣ በሜሴንጀር እና በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛዎች ለሚመጡ በብዙ መቶዎች ለሚቆጠሩ መንፈሳዊ ጥያቄዎች ምላሽ እና የምክር አገልግሎት ተሰጥቷል።
  • ይህን ዓመት 2012 ዓ.ም (2019/20) በቤተሰባችን አገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ ለየት ካደረጉት ነገሮች አንዱ መላው ቤተሰብ በአገልግሎት ላይ በቀጥታ በመሳተፉ ነው። ባለቤቴ ምኞቴ ክፍሌ ከመጋቢት (ማርች 2020) ጀምሮ ያሉትን እሁዶች በሙሉ በመለኮት ቤተክርስቲያን የሶሎ ዝማሬ አገልግሎት በመስጠት ላይ ስትሆን ልጃችን ቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ መሳሪያ በመጫወት እያጀባት ይገኛል። ሴት ልጃችን ፍቅር ያሬድ በአዲስ ልደት ቤተክርስቲያን የወጣቶች አገልግሎት ውስጥ በዝማሬ እያገለገለች ሲሆን አንዳንዴም በእሁድ የአምልኮ ፕሮግራም ላይ የእግዚአብሔርን ቃል ታስተምራለች።
  • የርቀት ትምህርት ሥልጠና በተመለከተ ያገኙና አሁንም በማግኘት ላይ ያሉ፦ በተለያየ አለም የሚኖሩ ወደ 110 የሚጠጉ አማኞች የጎልደን ኦይል አገልግሎት የሚሠጠውን የርቀት ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
  • በዚህ ዓመት “እፎይታ” በመባል የሚታወቀውና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈው በየዕለቱ የሚነበብ የጥሞና መጽሐፍ ሦስተኛ ክፍል “እፎይታ ሣልሳይ” በሚል ርዕስ ተጽፎ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
  • አገልግሎቱ በዋሽንግተን ዲ.ሲ፣ በቨርጂኒያ እና በሜሪላንድ አካባቢ ካሉ አብያተ-ክርስቲያናትና አገልግሎቶች ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ኢምባሲ አማካይነት የኢትዮጵያ መንግሥት ኮቪድ-19ን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረትና የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ለማስፈጸም በሚያደርገው ርብርብ በገንዘብና በሐሳብ ከፍተኛ እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛል።
  • በ2013 ዓ.ም (2020/21)፦
    • ያሉትን አገልግሎቶች በጥራትና በሥፋት ለማሳደግ
    • “የአዕምሮ መታደስ” በሚል አዲስ መጽሐፍ ለመጻፍና ለማሳተም
    • በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ወንጌልን ለማሰራጨትና ዜጎችን በሥነ-ምግባር ለመቅረጽ የሚያገለግል የአጭር ሞገድ (ሾርት ዌቭ) ሬዲዮ ፕሮግራም ሥርጭት ሊጀመር የሚቻልበትን ቅድመ ዝግጅት ለመጀመር።
    • በኦንላይን በስፋት የሚሰጡ አዳዲስና ነጠላ የሥልጠና ሞጁሎችን በማዘጋጀት ለማሠልጠን ታቅዷል
    • በአዲስ አበባ
    • ኢትዮጵያ የሚገኘውን የአገልግሎቱን እንቅስቃሴ በማሳደግ አዳዲስ የአገልግሎት መስኮችን ለመጀመር ታቅዷል።
የጎልደን ኦይል አገልግሎት (አሜሪካ) የ2012 ዓ.ም የሥራ እንቅስቃሴ PDF ዳውንሎድ ያድርጉ